A research consortium based in Europe EN FR አማርኛ

AAGE — Amhara Advocacy Group in Europe

Documentation, research and advocacy for civilian protection in Ethiopia's Amhara region.

In this issue  ·  No. 49  ·  June 2026 Last updated 18 June 2026

Ressources · Textes fondateurs

የሰብኣውያን፡መብቶች፡ዓለም፡አቀፍ፡ድንጋጌ

Déclaration universelle des droits de l’homme — texte intégral en amharique.

መቅድም

የቤተ፡ሰብእ፡አባላትን፡ዅሉ፡መሠረታዊ፡ክቡርነትንና፥እኩሎችና፡የማይነፈጉ፡መብቶቻቸውን፡ማወቅ፥የነጻነት፣የፍትሕና፡የዓለም፡ሰላም፡መሠረት፡ስለ፡ኾነ፤

የሰብኣውያን፡መብቶች፡መጣ፟ስና፡አለመከበር፥የሰው፡ልጅን፡ኅሊና፡ያስቈጡ፡አረመኔያውያን፡ድርጊቶችን፡ስላስከተሉ፤ዛሬ፡ደግሞ፥የሰው፡ልጆች፡ከፍርሀትና፡ከዕጦት፡ነጻ፡ኾነው፡የመናገርና፡የእምነት፡ነጻነታቸውን፡መጐናጸፍ፡የማንኛውም፡ሰው፡ዐቢይ፡ዐላማ፡ተብሎ፡የታወጀበት፡ዓለም፥እንሆ፥እውን፡ስለ፡ኾነ፤

የሰው፡ልጅ፥ጭቈናንና፡ጥቃትን፡ለመከላከል፡ሲል፥በመጨረሻ፡ደረጃ፥ለመሸፈት፡እንዳይገደድ፥ሰብኣውያን፡መብቶች፡በርትዕ፡ሥርዐት፡ሊጠበቁ፡ስለሚገባ፤

በሀገሮች፡መካከል፡የወዳጅነት፡ግንኝት፡መዳበርን፡ማበራታት፡ስለሚገባ፤

የተባበሩት፡መንግሥታት፡ሕዝቦች፥ስለሰው፡ልጅ፡መሠረታውያን፡መብቶች፣ስለሰው፡ልጅ፡ክቡርነትና፡ዋጋ፣ስለወንድና፡ሴት፡እኩልነት፡ያላቸውን፡እምነት፡በሥምረታቸው፡ስላጸኑና፥ኅብረ፡ሰብኣዊ፡እድገትን፡ለማምጣትና፡የተሻለ፡የኑሮ፡ደረጃን፡በላቀ፡ነጻነት፡ውስጥ፡ለማረማመድ፡ስለ፡ቈረጡ፤

አባላት፡መንግሥታቱም፥ከተባበሩት፡መንግሥታት፡ድርጅት፡ጋራ፡በመሳተፍ፥የሰብኣውያን፡መብቶችንና፡የመሠረታውያን፡ነጻነቶችን፡ዓለም፡አቀፍ፡አክብሮት፡ለማረጋገጥ፡ለገቻ፡ስለ፡ገቡ፤

ይህንም፡ለገቻ፡ሙሉ፡ለሙሉ፡ለመፈጸም፥እነዚህን፡መብቶችና፡ነጻነቶች፡በጋራ፡መረዳት፡የላቀ፡ጥቅም፡ስላለው፤

ጠቅላላው፡ጉባኤ፥እንሆ፥እያንዳንዱ፡ግለኛና፡እያንዳንዱ፡የኅብረ፡ሰብእ፡ሕዋስ፥ይህን፡ድንጋጌ፡የዘወትር፡መመሪያው፡በማድረግ፥በሀገራዊም፡ኾነ፡በአህጉራዊ፡ደረጃ፥በአባላት፡ሀገሮቹ፡ሕዝቦችም፡ኾነ፡በሀገሮቹ፡ሥልጣን፡ሥር፡በሚገኝ፡ግዛት፡ሕዝቦችም፡ጭምር፥በሚፈጸሙ፡ተከታታይ፡ክንዋኔዎች፥የነዚህን፡መብቶችና፡ነጻነቶች፡መከበር፡በማዳበር፥ዓለም፡አቀፍ፡ዕውቅናቸውንና፡ክብረታቸውን፡ለማረጋገጥ፥ለሕዝቦች፡ዅሉና፡ለሀገሮች፡ዅሉ፥የጋራ፡አፈጻጸም፡ደንብ፡ኾኖ፡ያገለግል፡ዘንድ፥ይህን፡የሰብኣውያን፡መብቶች፡ዓለም፡አቀፍ፡ድንጋጌ፡ዐወጀ።

አንቀጽ፡1

የሰው፡ልጆች፡ዅሉ፡ነጻ፥በክብርም፡በመብትም፡እኩል፡ኾነው፡ተወልደዋል።ማመዛዘንንና፡ኅሊናንም፡ታደለዋልና፥ርስ፡በርሳቸው፡በወንድማማችነትና፡በእኅትማማችነት፡መንፈስ፡ሊሳተፉ፡ይገባል።

አንቀጽ፡2

የዘር፣የቀለም፣የጾታ፣የቋንቋ፣የሃይማኖት፣የግዛት፡ወይም፡የሌላ፡አስተያየት፣የሀገራዊ፡ወይም፡የኅብረ፡ሰብኣዊ፣የሀብት፣የትውልድ፡ወይም፡የደረጃ፡አንዳች፡ልዩነት፡ሳይደረግ፥ሰው፡ዅሉ፡በዚህ፡ድንጋጌ፡በታወጁት፡መብቶችና፡ነጻነቶች፡ዅሉ፡ሊመ፟ካ፡ይችላል።ከዚህ፡ወዲያ፥አንድ፡ሰው፡አባል፡በኾነለት፥ሐራም፡ኾነ፣በዐደራነት፡የተሰጠ፣ራሱን፡የማይገዛም፡ኾነ፣አንዳች፡የእግዚእና፡እግድ፡ያለበት፡ሀገርም፡ኾነ፡ብሔር፡(ምድር)፥በግዛት፣ወይ፡በሥልጣን፣ወይም፡በአህጉራዊ፡ደረጃ፡መሠረት፡ምንም፡ዐይነት፡ልዩነት፡አይደረግበትም።

አንቀጽ፡3

ማንኛውም፡ሰው፡የሕይወት፣የነጻነትና፡የሰብኣዊ፡ደኅንነት፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡4

ማንም፡ሰው፡በባርነትም፡ኾነ፡በተገዥነት፡ሥር፡አይያዝም።ባርነትና፡የባሪያ፡ንግድ፡በማንኛውም፡መልክ፡የተከለከሉ፡ናቸው።

አንቀጽ፡5

ማንም፡ሰው፡ለሥቃይ፥ለጨካኝ፣ኢሰብኣዊና፡የሚያዋርድ፡እንግልት፡ወይም፡ቅጣት፡አይዳረግም።

አንቀጽ፡6

ማንም፡ሰው፥የትም፡ቢኾን፥በሕግ፡ፊት፡እንደ፡ሰው፡የመታወቅ፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡7

ዅሉም፡በሕግ፡ፊት፡እኩል፡ናቸው፤አንዳች፡አመሳሶ፡ሳይደረግባቸው፥የሕግን፡እኩል፡ከለላ፡የማግኘት፡መብትም፡አለላቸው።ይህን፡ድንጋጌ፡በመራመድ፡ከሚፈጸሙ፡አመሳሶዎችና፡ከአመሳሶ፡ቍስቈሳዎች፡ዅሉ፡የመከ፟ለል፡እኩል፡መብት፡ለዅሉም፡አለላቸው።

አንቀጽ፡8

ማንም፡ሰው፥በሕገ፡መንግሥትም፡ኾነ፡በሕግ፡የተከበሩለትን፡መብቶች፡በሚጥሱበት፡ድርጊቶች፡አንጻር፡ዅሉ፥ተገቢውን፡መፍትሔ፡ለማግኘት፡በሀገራዊ፡የፍትሕ፡ሥልጣን፡ፊት፡አቤት፡የማለት፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡9

ማንም፡አላግባብ፡ሊያ፟ዝ፣ሊታሰር፡ወይም፡ሊጋዝ፡አይችልም።

አንቀጽ፡10

ሰው፡ዅሉ፥መብትና፡ግዴታው፡በሚለ፟ይበትና፡የተከሰሰበት፡ወንጀል፡ትኽክለኛነት፡በሚነጥርበት፡ጊዜ፥ጕዳዩ፥ነጻ፡በኾነና፡በማያዳላ፡የፍርድ፡ችሎት፡በተሟላ፡እኩልነትና፡በይፋ፡እንዲታይለት፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡11

11.1) በሕግ፡በሚያስጠይቅ፡በደል፡የተከሰሰ፡ሰው፡ዅሉ፥ለመከላከያው፡የሚያስፈልጉትን፡ዋስትናዎች፡ዅሉ፡ባገኘበት፡ይፋ፡የፍርድ፡ሸንጎ፥በሕጉ፡መሠረት፡በደለኛነቱ፡እስካልተመሰከረበት፡ድረስ፥አስቀድሞ፡በንጽሕናው፡ሊታወቅ፡መብት፡አለለት።

11.2) ማንም፡ሰው፥ከማድረግም፡ኾነ፡ካለማድረግ፡በተነሣ፥የተከሰሰበትን፡ድርጊት፡ፈጸመው፡በተባለበት፡ጊዜ፥በሀገራዊም፡ኾነ፡አህጉራዊ፡ሕግ፡መሠረት፡ከወንጀል፡የማይቈጠር፡ድርጊት፡ቢኾን፥ወንጀለኛ፡ሊባል፡አይችልም።ድርጊቱ፡ከወንጀል፡የተቈጠረበት፡እንደ፡ኾነ፡ደግሞ፥በወቅቱ፡ተፈጻሚ፡ሊኾን፡ከሚገባው፡ቅጣት፡የከበደ፡አይፈጸምበትም።

አንቀጽ፡12

ማንም፡ሰው፥በግሉ፣በቤተ፡ሰብኡ፣በቤቱ፡ወይም፡በግንኝቶቹ፥ጣልቃ፡አይገ፟ባ፟በትም፤በክብሩና፡በጥሩ፡ስሙ፡አይጠ፟ቃ፟ም።ሰው፡ዅሉ፡ይህን፡ከመሰለ፡ጣልቃ፡ገብነትና፡ጥቃት፡በሕግ፡የመከ፟ለል፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡13

13.1) በያንዳንዱ፡ሀገራዊ፡ወይም፡የመንግሥት፡(የኹነት)፡ድንበር፡ውስጥ፥ሰው፡ዅሉ፡በነጻነት፡የመዘዋወርና፡የመኖሪያ፡ቦታውን፡የመምረጥ፡መብት፡አለለት።

13.2) ሰው፡ዅሉ፥ከራሱም፡ኾነ፡ከማንኛውም፡ሀገር፡የመውጣትና፡ተመልሶ፡የመግባት፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡14

14.1) የተጨቈነ፡ሰው፡ዅሉ፥በሌላ፡ሀገር፡ጥገኝነትን፡የመጠየቅና፡የማግኘት፡መብት፡አለለት።

14.2) በሕግ፡በሚ፟ገ፟ባ፟፡ለሚያስጠይቅ፡የወንጀል፡ድርጊትም፡ኾነ፡አንዳች፡የተባበሩት፡መንግሥታትን፡ዐላማና፡መመሪያ፡ለሚፃረር፡ድርጊት፡ይህ፡መብት፡አይውልም።

አንቀጽ፡15

15.1) ሰው፡ዅሉ፡ለሀገራዊነት፡መብት፡አለለት።

15.2) ማንም፡ሰው፡ሀገራዊነቱን፡አላግባብ፡አይገፈፍም፤ሀገራዊነቱን፡የመለወጥ፡መብቱም፡አይነፈገውም።

አንቀጽ፡16

16.1) ለትዳር፡የደረሱ፡ወንድና፡ሴት፥ዘር፣ትውልድ፡ወይም፡ሃይማኖት፡ሳይገድባቸው፥የመጋባትና፡ትዳር፡የመመሥረት፡መብት፡አለላቸው።ለጋብቻም፣በጋብቻ፡ዘመንም፣በፍቺም፡ባለእኩል፡መብት፡ናቸው።

16.2) ጋብቻም፡በትዳር፡መሥራቾቹ፡ነጻና፡ሙሉ፡ፈቃድ፡ይፈጸማል።

16.3) ቤተ፡ሰብእ፡የኅብረ፡ሰብእ፡ባሕርያዊና፡መሠረታዊ፡ከዋኝ፡አሐድ፡እንደ፡መኾኑ፡መጠን፥የኅብረ፡ሰብእንና፡የመንግሥትን፡ከለላ፡ሊያገኝ፡ይገባዋል።

አንቀጽ፡17

17.1) ሰው፡ዅሉ፥በግልም፡ኾነ፡በኅብረት፥ባለንብረት፡የመኾን፡መብት፡አለለት።

17.2) ማንም፡ሰው፡ቢኾን፡ንብረቱ፡አላግባብ፡አይወሰድበትም።

አንቀጽ፡18

18) ሰው፡ዅሉ፡የሐሳብ፣የኅሊናና፡የሃይማኖት፡ነጻነት፡መብት፡አለለት፤ይህም፡መብት፥•ሃይማኖትን፡ወይም፡እምነትን፡የመለወጥ፥•ብቻውንም፡ኾነ፡በኅብረት፥በግልም፡ኾነ፡በይፋ፥ሃይማኖቱን፡ወይም፡እምነቱን፥በትምህርት፣በገቢር፣በአምልኮና፡በአክብሮት፡የመግለጽ፡መብትን፡ይጨምራል።

አንቀጽ፡19

ሰው፡ዅሉ፥ያስተያየትና፡አስተያየትን፡የመግለጽ፡ነጻነት፡አለለት፤ይህም፡መብት፥•ማንም፡ጣልቃ፡ሳይገባበት፡አስተያየትን፡ለራሱ፡የማብጀት፡መብትንና፥•ከማንኛውም፡ማወራኛ፥አንዳችም፡ጠረፍ፡ሳያግደው፥መረጃንና፡ሐሳብን፡የመቀባበል፡መብቱን፡ይጨምራል።

አንቀጽ፡20

20.1) ሰው፡ዅሉ፥በሰላም፡የመሰ፟ብሰብና፡የመተባበር፡ነጻነት፡አለለት።

20.2) ማንም፡ቢኾን፡ያንዳች፡ኅብረት፡አባል፡እንዲኾን፡አይገደድም።

አንቀጽ፡21

21.1) በቀጥታም፡ኾነ፡በነጻ፡ምርጫ፡በተመረጡ፡ተወካዮቹ፡አማካይነት፥ሰው፡ዅሉ፡በሀገሩ፡ግዛት፡የመሳተፍ፡መብት፡አለለት።

21.2) ሰው፡ዅሉ፡በሀገሩ፡ውስጥ፡የመንግሥትን፡አገልግሎቶች፡እኩል፡የመጋራት፡መብት፡አለለት።

21.3) የሕዝብ፡ፈቃድ፡ለመንግሥት፡ሥልጣን፡መሠረት፡ይኾናል፤ይህም፡ፈቃድ፥ምስጢራዊ፡ወይም፡በተመሳሳይ፡ነጻ፡የምርጫ፡ኺደት፡በየጊዜው፡በዓለም፡አቀፍና፡በእኩል፡መረጣ፡በሚካኼድ፡እውነተኛ፡ኅርየት፡ይገለጻል።

አንቀጽ፡22

ሰው፡ዅሉ፥እንደኅብረ፡ሰብእ፡አባልነቱ፥የኅብረ፡ሰብኣዊ፡ደኅንነት፡መብት፡አለለት፤ለክብረቱና፡ለሰብእናው፡በነጻነት፡መበልጸግም፡ተፈላጊ፡የኾኑት፡ጥርየታዊ፣ኅብረ፡ሰብኣዊና፡ባህላዊ፡መብቶቹ፥በሀገራዊ፡ጥረትና፡በአህጉራዊ፡መስተጋብር፥እንዲሁም፡እያንዳንዱ፡ሀገር፡ባለው፡ድርጅትና፡ዐቅም፡መሠረት፥ሊሟሉለት፡ይገባል።

አንቀጽ፡23

23.1) ሰው፡ዅሉ፥የመሥራት፡መብት፣ሥራውን፡የመምረጥ፡መብት፣ፍትሓዊና፡ተስማሚ፡የሥራ፡ኹኔታ፡መብትና፡ከሥራ፡ፈትነት፡የመከ፟ለል፡መብት፡አሉለት።

23.2) ሰው፡ዅሉ፥አንዳች፡አመሳሶ፡ሳይደረግበት፥ለእኩል፡ሥራ፡እኩል፡ክፍያ፡የማግኘት፡መብት፡አለለት።

23.3) ሰው፡ዅሉ፥እንዳስፈላጊነቱ፥ሌላ፡ኅብረ፡ሰብኣዊ፡ዳረጎት፡ታክሎለትም፡ቢኾን፥ለራሱም፡ኾነ፡ለቤተ፡ሰብኡ፡ሰብኣዊ፡ክብረትን፡የሚያሟላ፡ኑሮን፡ለማረጋገጥ፥ፍትሓዊና፡ተስማሚ፡ደመ፡ወዝ፡የማግኘት፡መብት፡አለለት።

23.4) ሰው፡ዅሉ፥የጥቅሞቹን፡መጠ፟በቅ፡ያረጋግጥ፡ዘንድ፥የሠራተኛ፡ማኅበራትን፡የማቋቋምም፡ኾነ፡የመተባበር፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡24

ሰው፡ዅሉ፥የሥራ፡ሰዓትን፡ርዝመት፡የገደበና፡ደመ፡ወዝ፡የሚከፈልበት፡ወቅታዊ፡የዕረፍት፡ጊዜን፡ያሟላ፥የማረፍና፡የመዝናናት፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡25

25.1) ሰው፡ዅሉ፥ለራሱና፡ለቤተ፡ሰብኡ፡ጤንነትና፡ደኅንነት፥ምግብን፣ልብስን፣ቤትን፣ሕክምናን፡ተፈላጊ፡ኅብረ፡ሰብኣዊ፡አገልግሎትን፡ላሟላና፡ተገቢ፡ለኾነ፡የኑሮ፡ደረጃ፡መብት፡አለለት፤በሥራ፡ማጣት፣በመታመም፣ባካል፡መሰ፟ንከል፥በትዳር፡መፍረስ፣በእርጅና፡ወይም፡ከቍጥጥሩ፡ውጭ፡በኾኑ፡ልዩ፡ልዩ፡ምክንያቶች፡የሕይወት፡ዋስትናው፡ቢነካ፥የደኅንነት፡መብት፡አለለት።

25.2) እናትነትና፡ልጅነት፡ለልዩ፡ክብካቤና፡ርዳታ፡መብት፡አለላቸው።በትዳርም፡ኾነ፡ከትዳር፡ውጪ፡የተወለዱ፡ልጆች፡ዅሉ፥ያንኑ፡ኅብረ፡ሰብኣዊ፡ከለላ፡እኩል፡የማግኘት፡መብት፡አለላቸው።

አንቀጽ፡26

26.1) ሰው፡ዅሉ፥ለትምህርት፡መብት፡አለለት።ቢያንስ፡እስከ፡አንደኛ፡ደረጃና፡መሠረታዊ፡ዕርከን፡ድረስ፥ትምህርት፡በነጻ፡ይሰ፟ጣ፟ል።ትምህርት፡ግዴታ፡ይኾናል።ኪናዊና፡ሟያዊ፡ትምህርት፡በጠቅላላ፡እንዲሰ፟ጥ፟፡ይደረጋል፤ከፍተኛ፡ትምህርትም፡ለሚገ፟ባ፟ቸው፡ዅሉ፡እኩል፡ይዳረሳል።

26.2) ትምህርት፡ሰብእናን፡ሙሉ፡ለሙሉ፡ለማበልጸግና፡ሰብኣውያን፡መብቶችንና፡መሠረታውያን፡ነጻነቶችን፡አክብሮት፡ለማጠናከር፡ያለመ፡ይኾናል።በሀገሮች፣በዘርና፡በሃይማኖት፡ወገኖች፡መኻከል፡የሚኖረውን፡መረዳዳት፣መቻቻልና፡ወዳጅነት፡ያረማምዳል፤የተባበሩት፡መንግሥታትን፡የሰላም፡ማስጠበቅ፡ተግባሮችንም፡ያስፋፋል።

26.3) ወላጆች፡ለልጆቻቸው፡የሚ፟ሰ፟ጠ፟ውን፡የትምህርት፡ዐይነት፡አስቀድሞ፡የመምረጥ፡መብት፡አለላቸው።

አንቀጽ፡27

27.1) ሰው፡ዅሉ፥በማኅበረሰቡ፡ባህላዊ፡ሕይወት፡ውስጥ፡በነጻ፡የመሳተፍ፥በሥን፡የመደሰትና፡ከጥበባዊ፡ግሥጋሤና፡ከሚገኙበት፡ጥቅሞች፡ዅሉ፡የመጋራት፡መብት፡አለለት።

27.2) ሰው፡ዅሉ፥ደራሲው፡ወይም፡ፈጣሪው፡ከኾነባቸው፡ጥበባውያን፣ቀለማውያን፣ሥናውያን፡ምርቶች፡ዅሉ፡የሚገኙትን፡መንፈሳውያንም፡ኾኑ፡ሥጋውያን፡ጥቅሞች፡የማስጠበቅ፡መብት፡አለለት።

አንቀጽ፡28

ሰው፡ዅሉ፥በዚህ፡ድንጋጌ፡የተነገሩለት፡መብቶችና፡ነጻነቶች፡እውን፡የሚኾኑበት፡ኅብረ፡ሰብኣዊና፡አህጉራዊ፡ሥርዐት፡ሊመሠረትለት፡ይገባዋል።

አንቀጽ፡29

29.1) ሰው፡ዅሉ፥ሰብእናው፡በነጻነትና፡በምላት፡ለሚበለጽግበት፡ማኅበረ፡ሰብኡ፡ግዴታዎች፡አሉበት።

29.2) ሰው፡ዅሉ፥በመብቶቹና፡በነጻነቶቹ፡ራሱን፡በሚበጅበት፡ጊዜ፥የሌሎችን፡መብቶችና፡ነጻነቶች፡ለማስጠበቅና፥በሥልጡን፡ኅብረ፡ሰብእ፡ውስጥ፡የጨዋነት፣የሰላምና፡ያጠቃላይ፡ደኅንነት፡ትኽክለኞች፡ግዴታዎችን፡ለማሟላት፡ተብሎ፡በሕግ፡ለተደነገጉት፡እገዳዎች፡ብቻ፡ይገደዳል።

29.3) እነዚህ፡ነጻነቶችና፡መብቶች፡የተባበሩት፡መንግሥታት፡ድርጅትን፡ግቦችና፡መመሪያዎች፡በሚፃረር፡መንገድ፡አይውሉም።

አንቀጽ፡30

በዚህ፡ድንጋጌ፡ውስጥ፡የሰፈረ፡አንድም፡ቃል፥በድንጋጌው፡ውስጥ፡የተዘረዘሩትን፡መብቶችና፡ነጻነቶች፡ለመሻር፡ወዳለመ፡አደራረግ፡ለመግባትም፡ኾነ፡አንዳች፡ድርጊት፡ለመፈጸም፥ላንዳች፡መንግሥት፣ቡድን፣ወይም፡ሰው፡መብት፡ይሰጣል፡በሚል፡ድምዳሜ፡ሊተረጐም፡አይችልም።-ፍጻሜ-